አንዱንም አልነገርኩትም ነበር...
"ነይ" የአንድ ቃል መልዕክት ነው የምትልክልኝ ከዛ በኋላ ቦርሳዬን ይዤ መሮጥ ነው ወደቤቷ። ይቺ አንድ ቃል ብዙ ትርጉም እንዳላት ስለማውቅ ደቂቃ መቆየት ሀጥያት ይመስለኛል።
የጣፋጭ አይነት ገዛዝቼ ስደርስ እንደልማዷ ሶፋ ላይ ተኮራምታ ትጠብቀኛለች። ጫማዬን ወርውሬ አጠገቧ እቀመጥና እግሬ ላይ አስተኛታለሁ። ፀጉሯን እየደባበስኩ እጠብቃታለሁ።
አንዳንድ ግዜ ከሚንዠቀዠቅ እንባዋ እና ከሚተናነቃት ሳግ ውጪ ቃል ሳንለዋወጥ እንቆይና ሲበቃት ያመጣሁላትን ጣፋጭ እየበላች የባጥ የቆጡን እየቀባጠርን እንቆያለን።
አንዳንዴ ደግሞ የተላላኩትን መልዕክቶች እያስነበበችኝ ወይ የነገራትን ቀልድ ወይ ለየት ያለ አገላለፅ እያስታወሰች ታስነካዋለች።ከአመት በፊት ነው፤ በፈረደበት ቴሌግራም ነው የተዋወቀችው የተጣራ ሶስት ወር ያወሩ አይመስለኝም ስለትዳር እና የጡረታ ዘመናቸው አውርተው ጨርሰው ነበር።
ከዛ በኋላ ድንገት ድርግም ብሎ ጠፋባት። እኔም እያየኋት አጣኋት መኖር አቆመች "ምክንያቱን ባውቅ እኮ፣ ይሄንን ነው ያደረግሺኝ ቢለኝ ራሴን በደንብ እወቅስ አልነበር? ስንብት አይገባኝም ነበር?" እያለች በደንብ ራሷን አሰቃየች።
ለማፅናናትም የቸገረ ሁኔታ ውስጥ የከተተኝን፤ የኔን ቆንጆ ተጫዋች ጓደኛ ድባቴ ውሰጥ የከተተብኝን ሰውዬ እስኪበቃው ረገምኩት።
ይህ በሆነ በወሩ [አለም እንደሆነ ከመዳፍ ትጠባለች] ከሆነ ሰውዬ ጋር በስራ ትገናኝና አንድ አንድ ሲሉ ከሰውዬዋ ጋር አብሮ እንደተማረ በቅርብ እንደሚያውቀው ነገራት።
በድንገተኛ ህመም ከሞተ ወር እንደሆነው ጭምርእዛው ወድቃ ተጠርቼ ስሄድ ለቅሶ ካልደረስን ሞቼ እገኛለሁ አለች። እሺ ከወጣላት ብዬ ተያይዘን የትናየት ከተማ ሄድን። ከወር በኋላ ለቅሶ መድረስ ምን ይሉታል? ጠይቀን ጠይቀን ቤታቸው ሰንደርስ ከእናቱ በቀር ማንም የለም።
ኦና ቤት ታቅፈው ሲቆዝሙ አገኘናቸው ገና ስታያቸው እሪታዋን ጀመረች። እሳቸውም አላቃሽ ይጠብቁ ይመስል ተቃቅፈው አስነኩት።
እሳቸው ቢረጋጉም ስለሱ አንድ ነገር በነገሩን ቁጥር የሆነ ነገር ባሉ ቁጥር እሷ እህ እህ እያለች እያለቀሰች አስቸገረችን።
በኋላ የስራ ባልደረቦቹ መሆናችንን ብነግራቸውም አኳኋኗ ብዙ እንዳስጠረጠራቸው ፊታቸው ያስታውቅ ነበር። ሲመሻሽ እንደምንጠይቃቸው ቃል ገብተን ወጣን። (እሷ ከዛ በኋላ በገንዘብም ስትረዳቸው እየሄደችም ስታያቸው ነበር)
ስንመለስ እርሟን ያወጣች የተረጋጋች መስሎኝ ነበር። እሷም እንደሱ ብላኝ ነበር። የሆነው ግን ተቃራኒው ነው። ለአንድ ሳምንት ከቤቷ ሳትወጣ ለቅሶ ተቀመጠች ፊቷ እስኪጠቋቁር ድረስ አለቀሰች።
ወደስራ ስትመለስ ግጥም አድርጋ ጥቁር ለብሳ ነበር። ማን ሞቶ ነው ሲሏት የቅርብ ዘመድ ነው እያለች ሀዘን አከረረች። ከስድስት ወር በኋላ ጥቁር ልብስ ስታወልቅ በመጨረሻ ደህና የምትሆን መስሎኝ ነበር።
መጀመሪያ "ደግሜ ሌላ ወንድ እንደወንድ የምቆጥር አይመስለኝም" ስትል ሀዘን ነው ሲያልፍላት ደህና ትሆናለች ብዬ ነበር።
እሷ እቴ ፊቷ የማይፈታ ሌላ ሴት ሆነች እንኳን ልትሽኮረመም ቀርቶ።በሳምንት የሆነውን ቀን "ነይ" ብላ መልእክት ትልካለች። ሀሳቡ ግልፅ ነው። "ሀዘን ሳይገለኝ ድረሺልኝ አስተዛዝኚኝ" ነው።
ቶሎ ባልደርስ የምትሞት ይመስለኛል። ሀዘኗ አስር አመት ቢቆይ እንኳን (የሰይጣን ጆሮ ይደፈን) አጠገቧ ለመሆን ዝግጁ ነበርኩ።
ባለሱቁ እንኳን ለምዶኝ "ፓኬጅ" ብዬ text ካደረግኩለት ጣፋጩን አዘገጃጅቶ ይጠብቀኛል። ከሱ ተቀብዬ ስደርስ ዛሬም ሶፋዋ ላይ ናት። ተኮራምታ ፀጉሯን እየደባስኩ ዝም አልኳት።
"ቤ?" አለች በወፈረ ድምጿ
"ወዬ የኔ ቆንጆ?"
"ዛሬ ምን ትዝ እንዳለኝ ታውቂያለሽ?" አለች ትራሱን አጥብቃ አቅፋ
"እም"
“ለካ ብዙ ያልነገርኩት ነገር ነበር”
"ኧረ”
"እውነት.. እንደዛም ሆኖ እኔን ከመውደድ አላገደውም እኮ አይገርምም?"
"ምንድነው ያልነገርሽው?”
"ለምሳሌ ስለልጆቼ አልነገርኩትም" ማደጎ ያሉ የምታሳድጋቸው ሁለት ልጆች አሉ። ሰው ሁሉ ስነሱ ካወቀ የሚያከብራት አክብሮት በዛ ምክንያት ስለሚመስላት ለማንም አትናገርም
"እውነት?"
"ሙች! እሱን እንኳን ሳያውቅ እኮ ነው የወደደኝ”
"ሌላስ”
“ብዙ ሰው የሚቀናበትን ቅርንጫፍ የበዛበት እቅዴን አልነገርኩትም" የአንድ ሰው እድሜ የማይጨርሰው እቅድ ነው ያላት ስለእቅዷ እያወራች መማረክ እንደምትችል ልምዷ አስለምዷታል
"ብትነግሪውስ ኖሮ"
"የበለጠ ይወደኝ ነበራ ምን አይነት ድንቅ ሴት ናት ይል ነበር”
"ሌላስ?"
"ሌላ ደሞ ራሴን በራሴ ፈረንሳይኛ እንዳስተማርኩ አልነገርኩትም”
"ኧረ ባክሽ?”
"አይገርምሽም የራሴ የምላቸውን ኳሊቲዎች አንዱንም አልነገርኩትም ነበር እኮ"
"ግን እንዲሁ ወደደሽ አይደል? እና እሱ አይበልጥም?" ብዙ ሳትጋጋጪ እንደዚ ነኝ እንደዛ ነኝ ሳትዪ መውደዱ አይበልጥም?"
"እኮ እሱ እኮ ነው የገረመኝ! ግን በነገርኩት ኖሮ! በደንብ በወደደኝ ኖሮ! ግን ይቅርብኝ ሁሉም ባይሞትብኝ ኖሮ!"
ወሬው አብቅቷል
እዬዬዋ ቀጥሏል
እስከመቼ ይሆን?


Girls friendship need to be named other than just “friendship” , and everything you wrote went through my bones. Keep going!
አንቺ ግን በጣም ጎበዝ ነሽ ስነ-ፅሁፍ ላይ... እንዴ አንዴም ቆም ስል አላስታውስም ይሄን ሳነብ... ምንድን ነው ሚስጥሩ?👀